ከ338 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ህገወጥ ምርቶች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ338 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ምርቶች በህገወጥ መንገድ ተከማችተው መያዛቸው ተገለጸ።
ምርቶቹ የተያዙት የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንተርፖል፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሰራው የተቀናጀ ሥራ መሆኑ ተነግሯል።
በአዳማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በ23 ቦታዎች ምርቶቹ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ባለስልጣን፣ ፌዴራል ፖሊስ እና ጉምሩክ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዱ፤ መድሃኒቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ገበያ ሲገቡ ጥራታቸው፣ ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው ባለመረጋገጡ በህብረተሰቡ ላይ የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት እንደሚያስከትሉ አስገንዝበዋል።
በተለይም ሕገወጥ መድኃኒቶች ህይወትን እስከመንጠቅ የሚደርስ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ተናግረዋል።
ከህገወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ 19 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ተብሏል።
በሰአዳ ጌታቸው