Fana: At a Speed of Life!

መምህራን የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ናቸው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ዘርፍ ስብራቱን ለመጠገን እየተደረገ ባለው ሂደት መምህራን ለትውልዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ዘርፍ የ9 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፥ የትምህርት ስራ ሀገርን የማስቀጠል ጉዳይ ነው ብለዋል።

የትምህርት ስርዓት ከተበላሸ ሀገር መኖር አይችልም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሁሉም ዜጋ  ትምህርትና ፖለቲካን በመለየት የትምህርትን ስብራት መጠገን እንዳለበት አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት በትምህርት ዘርፍ ያጋጠሙትን ችግሮች በማስታወስ፤ በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ሁሉንም በአንድነት የሚያስተሳስሩ ተቋማት ናቸው ያሉት ብርሃኑ (ፕ/ር)፤ በተለይ ስብራቱን ለመጠገን እየተደረገ ባለው ጥረት መምህራን ከራሳቸው በላይ ለትውልዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንዳሉ ጠቁመዋል።

የትምህርት ዘርፉ የመደብ ልዩነትና የኑሮ ከፍታና ዝቅታ ተፅዕኖ ውስጥ እየወደቀ መሆኑን አንስተው÷ ኢ-ፍትሐዊ የትምህርት ስርዓትን ለመቀየርና ለጥራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ትምህርት ቤቶች እንዲጠገኑ ለማድረግ 54 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል የመማሪያ መጻሕፍት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በመድረኩ ላይ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የድርሻውን ለተወጡ 69 ለሚሆኑ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና አመራሮች የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.