የኮሙኒኬሽን ሥራን ዓላማ ተኮር ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ የኮሙኒኬሽን ሥራችንን ዓላማ ተኮር ማድረግ አለብን ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶር) አስገነዘቡ፡፡
“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሠራራት” በሚል መሪ ሐሳብ ለክልል እና ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው የዐቅም ግንባታ ስልጠና እንደቀጠለ ነው፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የበይነ-መረብ ዐውዱ የመረጃ ፍሠቱን ከአንድ ወደ ባለብዙ አቅጣጫ የቀየረ እና የመረጃ ሥርጭት ፍጥነቱንም በእጅጉ ያሳደገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሁኔታዎችን ያገናዘበ የመንግሥታዊ መረጃ ሥርጭት መኖር እንዳለበት ገልጸው፤ ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ሕዝቡን ለመድረስ የኮሙኒኬሽን ሥራችንን ዓላማ ተኮር ማድረግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም በስትራቴጂ መምራት እና ሁሉንም የተግባቦት አማራጮች በመጠቀም የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማሟላት እንደሚጠበቅ መግለጻቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡