Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፓኪስታን-ኢትዮጵያ የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን አባላት በኢስላም አባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጎብኝተዋል።

የቡድኑ አባላት በዚህ ወቅት በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር)÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በተለያዩ መስኮች መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መንግስታት መካከል ያለውን የፓርላማ ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

የሀገራቱ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አምባሳደሩ÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት ትብብር በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መቆም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የፓርላማ ወዳጅነት ቡድኑ አስተባባሪ አርሻድ አብዱላህ ቮህራ በበኩላቸው÷በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በንግድና ኢኮኖሚ ልማት ዘርፎችም ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ የወዳጅነት ቡድኑ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በመተባበር በተለያዩ ዘርፎች ትብብሩን ለማጠናከር በንቃት እንደሚሠራ ማረጋገጣቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.