የደም ማነስ ለገጠመው ፅንስ ደም መስጠት …
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የእናቶችና ፅንስ ህክምና ክፍል የደም ማነስ ያጋጠመው የአራት ወር ፅንስ ደም እንዲሰጠው በማድረግ የጽንሱን ህይወቱ ማትረፍ መቻሉን በሆስፒታሉ የእናቶችና ጽንስ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰዒድ አራጌ ገልጸዋል።
ህፃናት በማህፀን እያሉ እንደማንኛውም ሰው የደም ማነስን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎች ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ተናግረዋል።
የጤና እክል ገጥሟት ወደ ሆስፒታሉ የመጣች አንዲት ነፍሰ-ጡር እናት በተደረገላት ምርመራ ሽሉ የደም ማነስ ችግር እንደገጠመው የተደረሰበት በመሆኑ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
እናትየው ወደ ሆስፒታሉ ስትመጣ የዘገየች ቢሆንም በተደረገላት ክትትል የጽንሱን ህይወት በመታደግ ውጤታማና አስደሳች ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።
ሾተላይ ወይም አር ኤች ፋክተር በመባል የሚታወቀው ህመም መኖሩ ከታወቀ ህፃናት በማህፀን ሳሉ በሚደረግላቸው የህክምና ክትትል በተሳካ ሁኔታ ማዳን እንደሚቻል መታየቱን አብራርተዋል።
በመሆኑም የህክምና ባለሙያዎች እንዲህ አይነት ችግር ያለበት ፅንስ ካጋጠማቸው ለተጨማሪ ህክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መላክ የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩን አስገንዝበዋል።
ይህንን የህክምና ሂደት በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ማስተማር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዶ/ር ሰዒድ፤ እናቶች ከመጀመሪያ ፅንስ ሁለተኛውና ሶስተኛው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተረድተው በአፋጣኝ ክትትል በማድረግ ወደተቋሙ እንዲመጡ አመላክተዋል።
ዶ/ር ሳምሶን ከሃሊ በበኩላቸው፤ በዘመናዊ አልትራሳውንድ በመታገዝ ህክምናው መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በማህፀን እያሉ የደም ማነስ ችግር የሚገጥማቸውን ህፃናት ህይወት መታደግ ተችሏል ብለዋል።
እናቶች በእርግዝና ክትትል ወቅት የደም አይነታቸውን በመለየት መድሀኒት በ28ኛው ሳምንት በመውሰድ የችግሩን የመከሰት ዕድል ከ16 በመቶ ወደ 0 ነጥብ 3 በመቶ ገደማ መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ፅንስ የሾተላይ ችግር ያለበት መሆኑ ከተረጋገጠ በማህፀን ውስጥ እያለ ለራሱ በተዘጋጀ መርፌ አማካኝነት ደም የመስጠት ስራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
በእየሩስ ወርቁ