ባሕር ኃይል የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ክፍሉን በሚፈለገው ልክ ለማጠናከር እና ለሠራዊቱ ተጨማሪ ዐቅም ለመሆን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
ተቋሙ አሁን ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ሥራ፣ ዐቅም ግንባታ እና መሠረተ-ልማት ግንባታዎች ላይ የሠራዊቱን ወታደራዊ ዝግጁነት ለማሳደግ ራሱን በማጠናከር ደረጃ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶችም የሁሉም የክፍሉ አመራርና አባላት ጥረት ነው መባሉን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ እንዳሉት፤ ተቋሙ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎች አከናውኗል፤ አሁንም ክፍሉን ለማጠናከርና ለሠራዊቱ ተጨማሪ ጠንካራ ኃይል ለመሆን የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡