ቻይና በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በቻይና ብሔራዊ ማሽነሪ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ም/ፕሬዚዳንት ሊ ሻይዩ የተመራ የቢዝነስ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሀገራቱ በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ዘርፉን ለማዘመን ኩታገጠም እርሻ በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ለዚህም ሰፊ የግብርና ማሽነሪዎች ፍላጎት መኖሩን አንስተዋል፡፡
ስለሆነም ኩባንያዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎችን ለኢትዮጵያ ገበያ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
በግብርና ምርት ኤክስፖርት፣ በአነስተኛ መስኖ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና ማሽነሪ ምርትና በሌሎች የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው÷ለውጤታማ ሥራም የጋራ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሊ ሻይዩ በበኩላቸው በዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች ምርት፣ በግብርና ልማትና በግብርና ምርምር ላይ ያላቸውን ሰፊ ልምድ ለሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በትብብር እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡