Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ጉዞ መግታት የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም – ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገውን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ መግታት የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል የለም ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ።

ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በሠራዊቱ የግዳጅ ቀጠና ተገኝተው ተልዕኮ በመፈፀም እና ሥልጠና ላይ የሚገኙ የሠራዊት አባላትን አበረታትተዋል።

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገውን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ መግታት የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የሠራዊቱ የዝግጁነት ደረጃ አመላካች ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ታላቅ ዝና፣ታሪክና ክብር ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

ክብሯንና ዝናዋን እንደጠበቀች ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ደግም የዚህ ትውልድ በተለይም ደግሞ የሠራዊቱ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ሰሜን ምዕራብ ዕዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ፣ የህዝቦቿን ሠላም ለማደፍረስና ፈጣን የልማት ዕድገቷን ለመጎተት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ የተቀበሉ ተላላኪ ባንዳዎችን አስታግሷል ነው ያሉት፡፡

መቼም ቢሆን በኢትዮጵያ ክብር አንደማንደራደር ጠላቶቻችን ጠንቅቀው ያውቁታል ሲሉ አጽንኦት መስጠታቸውንም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

ሰሜን ምዕራብ ዕዝ በማንኛውም ጊዜ፤ በየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘር ጥቃትን መከላከል በሚያስችለው የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡

የሰራዊት አባላቱ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጁነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መስራትና ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ተልዕኳቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.