የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልልን አጀንዳ ተረከበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ አጠናቅቆ አጀንዳዎችን ተረክቧል።
ኮሚሽኑ ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በባሕርዳር ከተማ ሲያካሄድ የቆየውን የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት አጠናቅቋል።
የክልሉን ምክክር በበላይነት ሲያስተባብሩ የቆዩት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) እና ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም የክልሉን አጀንዳ ከባለድርሻ አካላት ተወካዮች በይፋ ተረክበዋል።
ላለፉት ሰባት ቀናት በክልሉ በተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከ6 ሺህ በላይ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በሒደቱ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የማህበረሰብ ወኪሎች እንዲሁም የልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም÷በአማራ ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትምስጋና አቅርበዋል።
በአንዷለም ተስፋዬ