በልጆች ላይ ትኩረት ያደረገ ”ናኦታ” የተሰኘ የአፋን ኦሮሞ መጽሔት ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በልጆች ላይ ትኩረት ያደረገና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚታተም ”ናኦታ” የተሰኘ የአፋን ኦሮሞ መጽሔት ዛሬ ተመረቀ።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ ተገኝተዋል፡፡
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷መገናኛ ብዙሃን የነገውን ትውልድ በተሻለ መልኩ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።
በተለይ ህጻናት የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽ መሆናቸው የሀገሪቷን ተንሳዔ እውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ገንቢ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
‘ናኦታ’ መጽሔት ልጆች ስለሀገራቸው ወጥ የሆነ አረዳድ እንዲኖራቸውና አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።
ለመጽሔቱ ተደራሽነት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አበክሮ መስራት እንዳለበት ጠቁመው÷ ሕጻናት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን በማበረታታት ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ የመንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማት የቅርብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
አቶ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው፥ በሕጻናትና በታዳጊዎች ላይ የሚጻፉ ጽሁፎች የጋራ ትርክት ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
መጽሔቷ በኢ-ልቦለዳዊና በልቦለዳዊ ይዘቶች እያዝናኑ የልጆችን ሥነምግባር ለማነጽ፣ ልጆች የንባብ ልምድን እንዲያዳብሩ ዓይነተኛ መሳሪያ ሆና ታገለግላለችም ብለዋል።
በለተይ ሕጻናትን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በቀላሉ በማስተዋወቅ ልጆች በእውቀትና ክህሎት እየበለጸጉ እንዲረዱ ለመጽሄቷ መጠናከር ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ ÷ ዛሬ የተመረቀው የመፅሄት ዓምዶቹ ሲቀረጹና ስያሜ ሲሰጣቸው የልጆችን ሥነ ልቦና፣ ግብረገብነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ አብሮነትን፣ አሳታፊነትንና ሌሎች ጉዳዮችን እንዲያካትት ተደርጎ መሆኑን አስረድተዋል።