በመዲናዋ በ7 ቢሊየን ብር የኢንዱስትሪ ክላስተር እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ7 ቢሊየን ብር የኢንዱስትሪ ክላስተር እየተገነባ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
የ2017 የአምራች ኢንዱስትሪዎች አውደ ርዕይ “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሄዷል።
ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶችን የሚዳስስ ባለድርሻ አካላት የተገኙበት ፓናል ውይይት መካሄዱ ተገልጿል።
ጃንጥራር አባይ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥አስተዳደሩ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህም ከተማ አስተዳደሩ በአቃቂ ክፍለ ከተማ በ93 ሄክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ7 ቢሊየን ብር በጀት እየተሰራ ያለው ይህ ክላስተር የገበያ፣ የኤግዚብሽን እና የውጭ ግብይት ሰንሰለት ያለው ዘመናዊ የክላስተር ልማት እንደሆነ ገልፀዋል።
ክላስተሩ ሲጠናቀቅ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በቀጣይ በሚዘጋጀው የመመልመያ መስፈርት ወደ ክላስተሩ እንደሚገቡ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።