Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ዜጎችን ለእንግልትና ስቃይ የሚዳርጉ አጋጣሚዎች እየተከሰቱ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በፍጹም ሥነ ምግባር፣ በሃላፊነትና ሀገርን በመውደድ ስሜት ሊተገበር እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቀረፀው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከውጭ ሀገር የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት÷የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሥርዓትንና ሕግን አክብሮ  መተግበር ከተቻለ የዜጎችን፣ የሀገርንና የተቋማትን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ይቻላል፡፡

ሚኒስቴሩ ሥነ-ምህዳሩን ምቹ በማድረግ ኤጀንሲዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ኢንዱስትሪውን ለመቀየር ብቁ የኤጀንሲዎች ስብስብ በማፍራት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በላቀ ትጋት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሚናቸውን በኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ሕጋዊ አሰራርን በማይከተሉ ኤጀንሲዎች ሳቢያ ዜጎችን ለእንግልትና ለስቃይ የሚዳርጉ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ መከሰታቸውን ጠቁመዋል፡፡

መሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል የዜጎችን ክብርና ደህንነት ማዕከል ያደረገ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ሥርዓት እውን ለማድረግ የአዋጅ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሕጋዊ አሠራርን ተከትለው ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡ ኤጀንሲዎችን እውቅና ለመስጠት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ኤጀንሲዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ የሚያግዝ ወጥ የሆነ አደረጃጀት በቀጣይ ለመፍጠር ታቅዷል ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.