የሆሳዕና በዓል እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሆሳዕና በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የሆሳዕና በዓል በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በዓሉ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት የእለቱን የቅዳሴ መርሐ ግብር በመከታተልና በሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ-ሥርዓቶች እያከበሩ ይገኛል።
ሆሳዕና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን÷ ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።
በተመሳሳይ የሆሳዕና በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል፣ የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
ዕለቱ የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት እሁድ ላይ የሚውል ሲሆን÷ የኢትዮጵያ ካቶሊክ እምነት ተከታዮች በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ያከብሩታል።
በዓሉ በፀሎት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና እና በሌሎች ሀይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።