ባለፉት 9 ወራት ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ ውጤት አስመዝግባለች – የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ውጤት ማስመዝገቧን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በትላንትናው ዕለት በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ 2017 የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ግምገማውን ተከትሎ በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገበውን ውጤት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
ባለፉት 9 ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ከ60 በላይ ዓለም አቀፍ፣ አኅጉር አቀፍና ቀጣናዊ ጉባዔዎችን ማስተናገድ መቻሉን አስታውሰው÷ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ብዙ ለውጥ የታየበት እንደሆነ አመልክተዋል።
መንግሥት ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚያስፈልጋቸውን መሰረተ ልማቶች ከማመቻቸት ጀምሮ በዲፕሎማሲያዊ ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችና ተቋማት የሰጡት ትኩረት ለውጤቱ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ቱሪዝም የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ዘርፍ እንደመሆኑ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ ተሣታፊዎችን ያሉን ጸጋዎች እንዲመለከቱና እንዲያስተዋውቁ ማድረግ የተቻለበት እንደሆነም ገልጸዋል።
ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ባሻገር የመዳረሻ ልማት ሥራዎችም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በስፋት ሲሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህም ነባር የቱሪዝም ሀብቶችን የማላቅና የማደስ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥትና የፋሲል ቤተ መንግሥት ዕድሳትን ለአብነት አንስተዋል።
አዳዲስ የመዳረሻ ልምቶችም በትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ÷ የገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ የተከናወኑ የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳትን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን አመላክተዋል።
በአድማሱ አራጋው