Fana: At a Speed of Life!

ዲጂታል የአሰራር ሥርዓት በማስፋት ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ዲጂታል የአሰራር ሥርዓት በማስፋትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ ስራ መከናወኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን የዘርፎች አፈጻጸም እና ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልከቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም÷ ዲጂታላይዜሽን ማስፋፋት፣ መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ማድረግ፣ የዘመነ የአሰራር ሥርዓትን መዘርጋት፣ ከሥራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ኢኖቬሽንን ማስፋፋት ከሚኒስቴሩ ተልዕኮዎች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም ከግል ዘርፍ ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው÷ በዲጂታል ዘርፍ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ቴሌብርን ጨምሮ በዲጂታል መንገድ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ባለፉት 9 ወራት ወደ 800 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መንቀሳቀስ መቻሉን አንስተዋል።

ይህም ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸው÷ የጂጂታል ሥርዓት በመዘርጋት ገንዘብ ለማሳተም የሚጠይቀውን ሰፊ ወጪ ለማስቀረት መቻሉንም ተናግረዋል።

በሰው ሀብት ልማትም የ5 ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼትቭ ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ወደ 688 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ተመዝግበው ሥልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸው÷ ከዚህም ውስጥ 270 ሺህ ዜጎች ሥልጠናውን አጠናቀው ዓለም አቀፍ ሰርቲፊኬት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

ይህም የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው በለጠ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

በዘርፉ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን አዳዲስ ሀገራዊ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.