Fana: At a Speed of Life!

የ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የዕዳ እፎይታ ስምምነት ላይ ተደርሷል – አቶ አሕመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር ሲደረግ በነበረው ድርድር የ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የዕዳ እፎይታ ስምምነት ላይ በመርህ ደረጃ መደረሱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀናት እንዲሁም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው፡፡

በዚህም ከአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈረምና ከእያንዳንዱ አበዳሪ ሀገራት ጋር ዝርዝር ውይይቶች እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡

የዕዳ ጫናን በመቀነስ ረገድ በዚህ ዓመት ትልቅ ውጤት መገኘቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ የገቢ አቅምና የወጪ ንግድ እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በግምገማው ላይ መመላከቱን አስረድተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የምንዛሪ ተመን በገበያ በመወሰኑ በገቢ ምርትና በማህበረሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ከፍተኛ የድጎማ በጀት መመደቡን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለምግብ ዘይትና ለመድሃኒት ከፍተኛ ድጎማ ማድረጉን ገልጸው፥ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ መደረጉን አንስተዋል፡፡

የግብርና ምርትና የምግብ አቅርቦትን በማሻሻል የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተረጋጋ ማህበራዊና ሀገራዊ ሁኔታ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምርታማነትንና የንግድ ስርዓትን ማሻሻል፣ ገቢንና ወጪ ቁጠባን እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አፈጻጸም ማሳደግ እንደሚገባም በግምገማው ላይ ከስምምነት መደረሱን አቶ አሕመድ ሺዴ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.