Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 9 ወራት የወጪ ምርቶችን በመጨመር ረገድ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 9 ወራት በስራ እድል ፈጠራ፣ በምግብ ዋስትናና የወጪ ምርቶችን በመጨመር ረገድ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸምን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፥ በመኸር እርሻ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ገልጸው፥ ከለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከሰብል ምርት ብቻ 505 ሚሊየን ኩንታል ከመኸር እርሻ መገኘቱን ጠቅሰው፥ ዘንድሮ 610 ሚሊየን ኩንታል መገኘቱን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት፡፡

በመስኖ ዘርፍ አምና 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ የተሸፈነ ሲሆን ዘንድሮ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 4 በመቶ አጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ለማስመዝገብ ማቀዷን የገለጹት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ ከእቅዱ 6 ነጥብ 1 በመቶውን በግብርናው ዘርፍ ለማሳካት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በበልግ፣ በመኸርና በመስኖ ከፍተኛ ስራ ለመስራት ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና በተለይም በሌማት ትሩፋት የእንቁላል፤ የዶሮ፣ የወተት፣ የማርና የአሳ ምርቶች ከፍተኛ ውጤት ማምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና ገበያው ላይ ተፈጥሮ የነበረው የምግብ ምርቶች የዋጋ ንረት ወደ 11 ነጥብ 8 በመቶ መውረዱን ገልጸው፥ ይህም ሀገራዊ ምርቱ ምን ያህል ወደ ገበያ እየገባ እንደሆነ ያመላክታል ብለዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት የቡና ምርት፣ አበባና ቅባት እህሎች በስፋት ለውጭ ገበያ የቀረቡ ሲሆን÷ ከዚህም የግብርናው ዘርፍ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር አስተዋጽኦ ማድረጉንና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በስራ እድል ፈጠራ፣ በምግብ ዋስትናና የወጪ ምርቶችን በመጨመር ረገድ ባለፉት 9 ወራት የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና መጫወቱንም ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.