የተሰጠውን ህገ-መንግስታዊ መብት በመጠቀም የጋራ ተጠቃሚነትን ማጠናከር ይገባል – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሰጠውን ህገ-መንግስታዊ መብት በመጠቀም የህዝቦችን አብሮ የማደግና የጋራ ተጠቃሚነትን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡
የስልጤ ብሔረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብት እውቅና ያገኘበት ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በክብረ በዓሉ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ በተደረገው የጋራ ጥረት የስልጤ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብትን ሊያገኝ ችሏል ብለዋል።
የመቻቻልና የመደጋገፍ ባህልን በማሳደግ ታሪክን፣ ቋንቋን፣ ወግና ባህልን ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በልዩነት ውስጥ አንድነትን በማጎልበት በባህልና ቋንቋ የተጀመረውን አብሮነትንና በጋራ የመልማት ርብርብ በድህነት ላይ መድገም እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡