ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በትብብር መስራት ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በተቀናጀ አግባብ ሕዝቡን ባለቤት አድርጎ መስራት ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ፡፡
”ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ” በሚል መሪ ሃሳብ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ እየተካሄደ ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በክልሉ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ የሚገታ እንቅፋት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ድርጊቱ በሕጋዊ መንገድ የተከናወኑ ሥራዎችን የሚያቃውስ እና ጥቂቶች ተጠቅመው ሌላው የሚጎዳበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
የግብርና ምርት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጪ እየወጣ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን÷ ይህም አምራች አርሶ አደሩ እንዳይጠቀም የሚያደርግና ሀገር ማግኘት ያለባትን ገቢ የሚያሳጣ ነው ብለዋል።
የኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን ሁለንተናተዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ግብረ ሃይሉ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ ማሳሰባቸውንም የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡