ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ሺህ 250 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ሺህ 250 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀናትና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ግምገማ ተካሂዷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ግምገማውን ተከትሎ በሰጡት ማብራሪያ÷ የመምህራን ክህሎት ማነስ፣ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የስርዓተ ትምህርት ችግር እና የመጻሕፍት አቅርቦት የትምህርት ዘርፍ ማነቆዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ወደ 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከህብረተሰቡ በመሰብሰብ ትምህርት ቤቶች እንዲሰሩና እንዲታደሱ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ይህን የትምህርት ንቅናቄ አጠናክሮ በማስቀጠል በገንዘብ፣ በአይነት እና በጉልበት ወደ 54 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በማሰባሰብ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ እና እንዲጠገኑ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ1 ሺህ 250 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 390 የሚሆኑ አንደኛና መለስተኛ ትምህርት ቤቶች እና 200 የሚደርሱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንም ገልጸዋል።
22 ሺህ ለሚደርሱ ትምህርት ቤቶች እድሳት መደረጉን በማንሳት÷ የመማር ማስረተማር ስራው ምቹ እንዲሆን እንደተቻለም አመላክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በከተማ ብቻ ይታወቅ የነበረው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ ወደ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲዳረሱ እየተደረገ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡