Fana: At a Speed of Life!

የባህር በር ጉዳይን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ተገምግሟል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የዲፕሎማሲ ዘርፉን አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች በርካታ ስኬቶች መመዝገቡን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ መድረክ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጓን እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተናገዷን እና የህብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧን አንስተዋል።

ከአጎራባች ሀገራት ጋር ከወደብ እና የባህር ጉዳይ ጋር በተገናኘ የነበሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት መቻሉን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ እንደተቻለም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎች የኢትዮጵያን አቅም እና ተጽእኖ ፈጣሪነት ይበልጥ እያጎለበቱ መሆናቸውን አንስተው÷ በኃይል መሰረተ ልማት ቀጣናውን ለማስተሳሰር ሰፋፊ ስራ ማከናወኗንም ጠቅሰዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይታጠር ለቀጣናው አቅም እንደሆነ በተጨባጭ የታየበት መሆኑን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበሩ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.