Fana: At a Speed of Life!

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተመዘገበው ስኬት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት 9 ወራት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል÷ባለፉት 9 ወራት እንደ ሀገር በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በሚኒስቴሩም ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡

በእያንዳንዱ ዘርፍ እድገት ሲመዘገብ በቀጥታ ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር እንደሚገናኝ ገልፀው÷እንደ ሀገር የተከናወነው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት ለ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ÷የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ አስረድተዋል፡፡

የዲጂታል ሥራን በማጠናከር 344 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገር ሥራ እድል መፍጠሩን ጠቁመው÷ በኮደርስ ኢንሼቲቭ 45 ሺህ ዜጎችን የዲጅታል ሥራዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችን የሥራ እድል ፈጠራ ስልጠናዎችን በመስጠት በአካባቢያቸው ያለውን ፀጋ እንዲመለከቱ ማድረግ መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡

በልምድ ሲሰሩ ለነበሩ ሙያ ፈጣሪዎች ሚኒስቴሩ እውቅና መስጠት መጀመሩን እና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 80 ሺህ የልምድ ባለሙያዎችን እውቅና ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሥራ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ÷የሥራ እድልን በመፈጠር ረገድ ከመንግስት በተጨማሪ ባለሃብቶችና ባለድሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.