በትግራይ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ አሰራርን መከተል ይገባል – ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ዘርፍን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራርን መከተል ይገባል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ ገለጹ፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በግብርና ስትራቴጂክ ትግበራ እቅድ ዙሪያ በመቐለ ውይይት አካሂዷል።
ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ በዚህ ወቅት አንደገለፁት÷የግብርና ዘርፉን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂክ አሰራር መከተል ይገባል።
የግብርና ልማትን ውጤታማ ለማድረግ በነበረው ስትራቴጂና ፖሊሲ መቀጠል የማይቻል በመሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማከል ውጤታማ ለመሆን መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመሆኑም የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት በመጠበቅ፣ ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተልና የተቀናጁ ጥረቶችን በማከናወን ማልማት እንደሚገባ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚሁ ዙሪያ የተዘጋጀውን የስትራቴጂክ አተገባበር ውጤታማ ለማድረግና የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል በቅንጅት መስራት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው÷የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ እያሱ አብረሃ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የስትራቴጂው ትኩረት ግብርናን ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡