Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ቤላሩስ በባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ስፖርት ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ያለመ ምክክር አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ከቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ሪዚሄንኮቭ ጋር በሁለትዮሽ የሥራ ማዕቀፍ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የሁለትዮሽ የሥራ ማዕቀፉ፤ በባህል፣ በስፖርትና በኪነጥበብ ዘርፍ ሀገራቱ በትብብር እንዲሠሩ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሚኒስትሮቹ ውይይት፤ ባህል፣ ስፖርትና ኪነጥበብ ዘርፎችን በመጠቀም የሕዝቦችን አብሮነት ለማሳደግና የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥር ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ወደ ቤላሩስ አቅንተው ሀገራዊ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም የቤላሩስ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች በኢትዮጵያ እንዲቀርቡ እና የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ልምዷን ለቤላሩስ እንድታካፍል እና ከቤላሩስ ደግሞ የቅርጫት ኳስ ስፖርትና የዋና ስፖርት ልምድን እንድትቀስም ከስምምነት መደረሱን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያና የቤላሩስ ቴክኒካል ባለሙያዎች በዲፕሎማቲክ ቻናል የጋራ የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት መሥራት እንዳለባቸው ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.