በ63 ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ላይ በ63 ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና አመራር ሰጪነት በርካታ ከተሞች ጽዱና ምቹ የመኖሪያና የማምረቻ ማዕከል እየሆኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለሁሉም ዘርፎች እየሰጡ ባሉት የአመራር ድጋፍና ክትትል እንዲሁም በሕዝቡ ተሳትፎ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መኖሩን ነው የገለጹት።
ይህ ዘመን የከተሞች የህዳሴ ዘመን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ የኮሪደር ልማቱ የበርካታ ከተሞችን መሠረተ ልማት በማሻሻል አካታች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተገኘውን ተሞክሮውን በማስፋት በአሁኑ ወቅት በ63 ከተሞች የኮሪደር ልማቱ እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በዚህም በብዙ ከተሞች የተጎሳቆሉና በአረንቋ ውስጥ የቆዩ ሰፈሮች ሙሉ ለሙሉ ተቀይረው ዘመናዊ፣ ውብና ምቹ የመኖሪያ፣ የሥራና የመዝናኛ ማዕከል እየሆኑ ነው ብለዋል።
በኮሪደር ልማቱ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የመብራትና ሌሎችም የአገልግሎት መሰረተ ልማቶች በስፋት ተገንብተው ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም መንግሥት በሁሉም አካባቢ ፍትሐዊ ልማትን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን ጉዞ የሚያሳከ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ከለውጡ በፊት 74 በመቶ የከተሞች ክፍል ደረጃውን ያልጥበቀና የተጎሳቆለ እንደነበር በማውሳት፥ ከለውጡ ወዲህ በተከናወኑ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ሥራዎች መሻሻል መጥቷል ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን የፈጠራ፣ የምርምር፣ የአዳዲስ ሀሳቦች መፍለቂያ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ከሸማችነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ዕድል እንደፈጠረ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የከተማ የአረንጓዴ ሽፋንም 5 በመቶ ከነበረበት ወደ 22 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቅሰው÷ከኮሪደር ልማት ባሻገር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተፋጠኑ ነው ብለዋል።