አቶ ሙስጠፌ የጅግጅጋ ኮሪደር ልማት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ በጅግጅጋ ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ከተቋራጭ ድርጅቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እና አጋር አካላትም ተገኝተዋል፡፡
በውይይታቸውም በጅግጅጋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የጅግጅጋ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን እያከናወኑ የሚገኙ ተቋራጮችና አማካሪ ኩባንያዎች ለርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት አቅርበዋል።
አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ተቋራጮቹ ያቀረቡትን ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ ለሥራው ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የግንባታ ኩባንያዎቹ ፕሮጀክቱን በአንድ ወር ጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲያጠናቅቁም አቅጣጫና መመሪያ ሰጥተዋል።