የወጪ ንግድ ዘርፍ አፈጻጸምን በዓመቱ መጨረሻ 7 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ እየተሰራ ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የወጪ ንግድ ዘርፍ አፈጻጸም ባለፉት 9 ወራት ከተመዘገበው 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በዓመቱ መጨረሻ 7 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀምና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አፈፃፀም የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ከሀገራዊ የብልጽግና ራዕይ አኳያ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር እውን ለማድረግ በ5ኛው የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ አስተማማኝ ስራዎች መከናወኑንም አንስተዋል።
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን የሙከራ ንግድ ለማስጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
ስኬቶቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፈጠራቸው ምቹ ሀገራዊ አውድ ምክንያት የተመዘገበ እንደሆነም አመላክተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በኢትዮጵያ ለውድድር ምቹ የሆነና ዘመናዊ የንግድ ከባቢን ለመፍጠር የተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በቅርቡ ጄኔቫ በተካሄደው 5ኛው የድርጅቱ የስራ ቡድን ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ የተካሄደው የድርድር ሂደት ስኬታማ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
የንግድ እቃዎችንና አገልግሎቶችን ጥራት ለማስጠበቅ በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀው የጥራት መንደርና መሰረተ ልማት ኢትዮጵያ ለምርት ጥራት የሰጠችውን ትኩረት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ለህዝቡ ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል እንደሆነ መግለፃቸውንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡