የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ 5 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አስታወቀ፡፡
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ተቋሙ ላለፉት ሶስት ዓመታት የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለማረጋገጥና የአስቀማጮችን ደህንነት ለማስጠበቅ ውጤታማ ስራ ሲከውን መቆየቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5 ነጥብ 89 ቢሊየን ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው፥ ከዚህም ውስጥ 88 ነጥብ 29 በመቶው ከአረቦን እንዲሁም 11 ነጥብ 71 በመቶው ከኢንቨስትመንት ስራ የተሰበሰበ ነው ብለዋል።
ከባንኮች እና ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተሰበሰበው የአረቦን ክፍያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትና አቅሙን ለማሳደግ የሰበሰበውን አረቦንና ተመላሽ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶችን መልሶ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢንቨስትመንት ክምችቱ 12 ነጥብ 11 ቢሊየን ብር መድረሱን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ የመረጃ አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን የመገንባት፣ የባለሙያ አቅምን የማሟላትና ሌሎች ስራዎች መሰራታቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በታምራት ደለሊ