Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የትንሳዔ በዓል ግብዓቶች በበቂ መጠን ለገበያ እየቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለትንሳዔ በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ ለፋና ዲ ጂታል እንዳሉት÷ በበዓሉ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

በተለይም በክልሉ በየደረጃው ኮሚቴ ተዋቅሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

ከመደበኛ ገበያ በተጨማሪ በባዛሮችና ኤግዝቢሽኖች እንዲሁም በ557 የቅዳሜና እሑድ ገበያዎች የበዓል ፍጆታ እቃዎች ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ለበዓሉ 220 ሺህ በላይ የቁም እንስሳት፣ 230 ሺህ ፍየሎች እና 200 ሺህ በጎች በአጠቃላይ 630 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

10 ሚሊየን ዶሮዎች እና 40 ሚሊየን በላይ እንቁላል ለበዓሉ በተለያዩ ገበያዎች ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡

ለበዓሉ 200 ሺህ ኩንታል የስንዴ፣ ገብስና በቆሎ ዱቄት እንዲሁም 450 ሺህ ቶን በላይ አትክልትና ፍራፍሬ በተመጣኝ ዋጋ ለገበያ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የፓልም ዘይት መሰራጨቱን ጠቁመው÷ ፈሳሽ ዘይቶችም ከፋብሪካዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በስፋት ለገበያ መቅረባቸውን አንስተዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ለትንሳዔ በዓል በቂ ምርት መኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሸምት ያስገነዘቡት ም/ሃላፊው÷ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

ዜጎች ለበዓሉ ጊዜ ያለፈባቸውና ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸው ምርቶችን እንዳይገዙ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም ደረጃዎች የተዋቀረው ኮሚቴ የበዓል ገበያው በተገቢ ሁኔታ እንዲሳለጥ አስፈላጊውን ቁጥጥር እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.