የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የባንኮችን የቁጠባ አቅም ማሳደጉ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ግኝትንና የባንኮችን የቁጠባ አቅም ማሳደጉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፋይናንስ ዘርፍ ስኬታማ ሀገራዊ የፖሊሲ ለውጥ መሆኑን የገለጹት አቶ አቤ÷ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን በመከተል በመደበኛና በትይዩ ገበያ መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ማጥበብ መቻሉን ተናግረዋል።
ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም ለተለያዩ ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ ነው ብለዋል።
ከማሻሻያው በፊት የነበረው የፋይናንስ ስርዓት የሀገር ውስጥ ምርትን ለውጭ ገበያ አቅርቦ ምንዛሪ ማግኘትን የማያበረታታ እንደነበርም አውስተዋል።
አሁን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፈጠረው ምቹ ዕድል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እየጨመረ መሆኑንም ተናግረዋል።
እየተገኘ ያለው ስኬት ማሻሻያው በጥራትና በውጤታማነት እየተመራ መሆኑን እንደሚያሳይ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ÷ ይህም ትክክለኛ የእድገት መንገድ መሆኑን አመላክተዋል።
ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ማምጣቱ የፖሊሲ ትግበራውን ትክክልኛነት ያሳየ መሆኑን ገልጸው÷ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 125 ቢሊየን ብር ገቢ እንዳገኘና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ ማስመዝገቡን ተናግረዋል።