Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ኮደርስ ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ ለማሳካት ትልቅ ሚና አለው – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወቅቱን የዋጀ ዜጋ በመፍጠር ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ ለማሳካት ትልቅ ሚና አለው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ክልላዊ አፈፃፀም ግምገማ እና የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢኒሼቲቩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ከተዋወቀ ጊዜ ጀምሮ በርካቶችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ክህሎት ጨብጦ፤ ብቃትና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ስኬታማና አሸናፊ የመሆን ፍላጎቱና ዝግጁነቱ ላለው ዜጋ የቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።

ስልጠናው የዲጂታል ክህሎት በማስጨበጥ፣ ተወዳዳሪ፣ ስራና ሀብት በመፍጠር ከራስ አልፎ ለሀገር መትረፍ የሚችሉ አምራች ዜጎችን ለማፍራት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በክልሉ በርካቶች ስልጠናውን ተከታትለው ማጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፤ ስልጠናውን ያልወሰዱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠናውን በመከታተል የዲጂታል ክህሎታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት በተለያዩ ዘርፎች መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት መጨበጥ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዘመኑ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመዘጋጀት በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ፤ በጊዜና ቦታ ሳይገደቡ ተመዝግበው ስልጠናውን እንዲወስዱም ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.