Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሥራን እንደሚደግፍ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ግጭትን የመከላከልና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚደግፍ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊነት ጉዳዮች ማስተባበሪያ አስታውቋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊነት ጉዳይ አስተባባሪ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም፤ ግጭቶችን ለመከላከል እና ሀገራዊ የሰላም ግንባታን ለማሳደግ በትብብር መሥራት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ግጭትን መሠረት አድርጎ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ተቋማትና የተለያዩ ሴክተሮች ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሕዝቦችን ትስስርና አንድነት በሚያጠናክር ብሎም ዘላቂ ሰላምን በሚያፀና መልኩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ እና የተረጋጋ ሕይወት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መከላከልና ሲፈጠሩም በሰላማዊ ውይይት መፍታት ሰፊ ጥረት የሚጠይቅ እና ልዩ ልዩ ባህሪያት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራት ተገቢ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊነት ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚስ አልካብሮቭ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ግጭትን ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አድንቀዋል፡፡

እየተከናወኑ ያሉ ግጭትን የመከላከልና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.