Fana: At a Speed of Life!

2 ሺህ መካከለኛ ደረጃ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ሺህ የሚሆኑ መካከለኛ ደረጃ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ10 ሺህ በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እድሳት መከናወኑን ጠቅሰው፤ የስፖርት ልማትን ስኬታማ ለማድረግ ህፃናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶችን ማዕከል በማድረግ መካከለኛ ደረጃ ያላቸው ሶስት በአንድ የሚባሉ ስታዲየሞች ተገንብተዋል ብለዋል።

ከለውጡ በፊት ተጀምሮ ሲጓተት የነበረው የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ቀሪ ስራ ተለይቶ በሁለት ሎት ተከፍሎ ለኮንትራክተሮች መሰጠቱንም ገልፀዋል።

በየክልሉና አካባቢው ያሉ ከለውጡ በፊት ተጀምረው ሲንከባለሉ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ መጀመሩን አንስተው፤ በክልሎች አዳዲስ ትላልቅ ስታዲየሞች ግንባታ መጀመሩንም አስረድተዋል።

ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በብሪክስ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኪናዊ ውጤቶችና ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ የባህል ዲፕሎማሲን ማጠናከር የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በግንቦት ወር የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ እንደሚደረግ አንስተው፤ ስፖርት ማህበራዊ ትስስርንና አብሮነትን ለማጠናከር ያለውን ሚና ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ባህላዊ እሴቶች ለብሪክስ አባል ሀገራት ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኗንም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.