Fana: At a Speed of Life!

ከ22 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መሳተፋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ22 ሚሊየን በላይ ወጣቶች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ማከናወናቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀናትና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ግምገማ ተካሂዷል፡፡

ሚኒስትሯ እንደ ተቋም በተከናወኑ ተግባራት ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ወጣቶችና ሴቶች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዜጎች ትኩረት የሚሰጥ ፖሊሲን እንደምትከተል ጠቅሰው፤ በዚህ ፖሊሲም በተለያዩ ሀገራት ችግር ውስጥ የቆዩ ከ44 ሺህ በላይ ዜጎች ከስደት ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከ22 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ መስኮች ተሳትፈው 50 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎችን አገልግለዋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወጣቶቹ የተሳተፉባቸው መስኮች የዐቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ደም ልገሳ፣ ትራፊክ ሕግ ማስከበርና በክረምት ተማሪዎችን ማስተማር መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ከ30 ሺህ በላይ ዐቅመ ደካሞችን፣ እናቶችን፣ አረጋውያንና ሕጻናትን ከጎዳና ላይ በማንሳት ወደ መደበኛ ሕይዎታቸው እንዲመለሱ ማስቻላቸውንም አክለዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚደርሱ የሕጻናት መብት ጥሰቶችን ማወቅና መከታተል የሚያስችል ብሎም ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የዲጂታል አሠራር መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማኅበራዊ ዕድገት መኖሩን የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.