ችግሮችን ለመቋቋም የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ውጤት እያመጡ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም መተግበር የተጀመሩ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችና የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና የዘርፎች ዕቅድ አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የፌዴራል ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ሀገራዊ ሪፎርሞች አከናውኗል፡፡
መንግሥት የወሰዳቸው ሀገራዊ ሪፎርሞች እና የፖሊሲ ለውጦች ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የተቋማትን የመፈጸም አቅም አሳድጓል ብለዋል፡፡
መንግሥት ህዝብ ውስጥ ሆኖ የሚሰራ እና ህዝብን የሚያዳምጥ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰብዓዊ ልዕልና እና ሀገራዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል የሚል ጽኑ መርህ እንዳላትና ይህም በሁሉም አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተደማጭነት ያጎለበቱና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
በቀጣይም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና ምርታማነትን ማሳደግና የተፅዕኖ አድማስን የማስፋት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተረጂነትን በማስወገድ በሁሉም መስክ ራሷን እንድትችል እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም መቋቋም የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው ብለዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የበጋ መስኖና ሌሎችም ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችና የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በበኩላቸው፥ በለውጡ መንግሥት የተከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ሪፎርሞች የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያለመልሙ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለላቀ ስኬት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡