Fana: At a Speed of Life!

ከፍርድ ቤትና ከፖሊስ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ስኬታማ አፈፃፀም ተመዝግቧል – የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፍትህ ዘርፍ ከፍርድ ቤትና የፖሊስ ተቋማት ጋር የተሻለ ቅንጅት በመፍጠር ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፍትሕ ዘርፉን እንቅስቃሴ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ የወንጀል መዝገቦችን በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ከፍርድ ቤትና ከፖሊስ ተቋማት ጋር የተሻለ ቅንጅት በመፍጠር ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን አንስተው፥ ለሌሎች የፌደራል መንግስት ተቋማት ውጤታማ የፍትሐ-ብሔር፣ የሕግ ማርቀቅ፣ የሕግ ምክር እና ጥናት የድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁ ሕግጋትን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ በአፈፃፀም ኦዲት ሥርዓት ድጋሚ ዳሰሳ መደረጉን እና የሕግ-የበላይነትን ለማረጋገጥ የወጡ ሕግጋት በተጨባጭ ስራ ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

የሚኒስቴሩን አሰራር በማሻሻል ሂደት ተቋማዊ የቅሬታ ሥርዓትን በመፈተሽ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑ ተግባራት ተከናውነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤትና የሌሎች ባለድርሻ ተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳለጥ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የማህበረሰብ ፍትሕን ለማጎልበት ክልሎች በባህላዊ ፍርድ ቤት ላይ ሰፋፊ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.