በሱዳናውያን ባለቤትነት የሚመራ የሰላም ሂደት በሀገሪቱ ያለውን ቀውስ ለመፍታት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በሱዳን ጉዳይ በለንደን እየተካሄደ ባለው ጉባኤ እየተሳተፈ ይገኛል።
በጉባኤው በሰብአዊ ዕርዳታ፣ የተኩስ አቁም ስምምነትን በማረጋገጥ እና የሱዳንን ግጭት በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ልዑክ በዚህ ወቅት፤ በሱዳናውያን ባለቤትነት የሚመራ የሰላም ሂደት አስፈላጊነትን በማንሳት÷ ሰላማዊ ዜጎችን ለመታደግ እና የሰብአዊ ዕርዳታን ያለ ዕንቅፋት ለማድረስ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን እና ስደተኞችን ለሚያስተናግዱ ጎረቤት ሀገራት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያሳድግ በማሳሰብ፤ የሰብአዊ ቀውሱን ለመቅረፍ ቀጣይ የሀብት ማሰባሰብ ስራን ይጠይቃል ብለዋል።
ልዑኩ በቀጣናው በሚገኙ አጋር አካላት ድጋፍ በሱዳናውያን የሚመራ የፖለቲካ ሽግግር አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ÷ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ የሰላም አካሄድ እንዲኖር መምከሩን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
እንግሊዝ፣ አውሮፓ ህብረት፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን እና አፍሪካ ህብረት በጋራ ያዘጋጁት ኮንፈረንሱ÷ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የ14 ሀገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች መሳተፉ ተጠቁሟል።