ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው- በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የጀመረችው ሪፎርም በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ማስቻሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትሮች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት የለውጡ መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን መተግበሩን ገልፀው፤ በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡን አንስተዋል።
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ በርካታ ውጤቶችን እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን እና አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ለአብነት ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መመዘኛ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አስችለዋል ነው ያሉት።