በበዓላት ወቅት የሚደርስን የማጭበርበር ወንጀል እንዴት መከላከል ይቻላል?
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበዓላት ወቅት በዲጂታል ምህዳሩ ውስጥ ከፍተኛ የሚባሉ የማጭበርበር እንቅስቃሴዎች ይስተዋላሉ።
በተለይ ለወዳጅ ዘመዶቻችን ስጦታዎችን ለመግዛት በተለያዩ መንገዶች ከፍተኛ ግብይቶችን የምናከናውንበት ወቅት መሆኑን ተከትሎ አጭበርባሪዎችም ይህንን እድል ለመጠቀም የተጠና እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ወቅት ነው።
በዚህ ወቅት አጭበርባሪዎች የተለያዩ መንገዶችን የሚጠቀሙ ሲሆን÷ ከእነዚህ መንገዶች መካከል፡-
👉በኢ-ሜይል (አጭር የጽሑፍ መልዕክቶችን) በመላክ የሚፈጸም ማጨበርበር፣
አጭበርባሪዎች በዚህ መንገድ ጥቃት ለማድረስ የሚያግዛቸውን አጥፊ ተልዕኮ ያላቸውን ሊንኮች እንዲከፍቱና የክፍያ ዝርዝሮችን እንዲያስገቡ በመጠየቅ ጥቃቶችን ያደርሳሉ። በተለይ በተጠቂያቸው እምነትን ለማግኘት የታዋቂ ተቋማትን ስም ይጠቀማሉ፣
👉የበጎ አድራጎት ሥራ በማስመሰል የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች፣
በበዓላት ወቅት የበጎ አድራጎት ስራዎች ይጨምራሉ። አጭበርባሪዎችም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በመኮረጅ እና የድጋፍ ጥያቄዎችን በኢ-ሜይል ወይም በሌሎች አመራጮች በመላክ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ስለጨመሩ ድጋፍ ከማድረግዎ በፊት፣ የድርጅቱን ህጋዊነት ያረጋግጡ።
👉ቅናሽ የጉዞና የማረፊያ ዋጋ ያቀረቡ በማስመሰል የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች፣
በበዓላት ወቅት ቤተሰብ ዘመድ ለመጥየቅና አብሮ ለማሳለፍ የሚደረጉ የጉዞ እንቅስቃሴዎች ይጨምራሉ። ይህን ሁኔታም አጭበርባሪዎች በዝቅተኛ ዋጋ የማረፊያ እና የትራንስፖርት ዋጋ ያስተዋውቃሉ።ምንም እንኳ ይህ ሁኔታ አጓጊ ቢሆንም ስለትክክለኛነቱ መለስ ብሎ ማሰብና ማረጋገጥ ይገባል።
👉ከክፍያ ጋር የተያያዙ ማጭበርበሮች፤
አጭበርባሪዎች ሰዎች በበዓላት ወቅት ትኩረታቸው በበዓል ጉዳዮች ስለሚወሰድ ጥንቃቄ እንደሚቀንስ ያውቃሉ። ይህን ጊዜ አጭበርባሪዎች የከፈልናቸውን ክፍያዎች እንዳልከፈልን ሳይከፍሉን ደግሞ ክፍለናል ብለዉ በዲጂታል የክፍያ አመራጭ ሊያጭበረብሩን ስለሚችሉ ክፍያዎችን ስንፈጽምና ስንቀበል በጥንቃቄ ልናድረግ ይገባል።
#የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር