“በአማራ ክልል የሚገኝ ታጣቂ ቡድን ለምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳውን አስገብቷል”- መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሚገኝ ታጣቂ ቡድን ባሳለፍነው ሣምንት አጀንዳውን ለምክክር ኮሚሽኑ አስገብቷል ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
“አጀንዳውን ለኮሚሽኑ ያስገባው ቡድን ማን ነው?” ተብሎ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለቀረበላቸው ጥያቄ ዋና ኮሚሽነሩ በሰጡት ምላሽ፤ “ማንነቱን መግለጽ የምንችለው ቡድኑ ፈቃዱን ሲሰጠን ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
አሁንም የታጠቁ ኃይሎች አጀንዳዎቻቸውን በወኪሎቻቸው አማካኝነት ማቅረብ እንደሚችሉ እና ኮሚሽኑም አጀንዳዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በባሕርዳር ከተማ ሲያካሄድ የቆየውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ማጠናቀቁ ይታወሳል።
በሒደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የማህበረሰብ ወኪሎች እንዲሁም የልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች መሳተፋቸው ይታወሳል።
በአመለወርቅ መኳንንት