የብዝኀ ሕይወት ጥፋትንና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብዝኀ ሕይወት ጥፋትን እና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ አፋጣኝ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል ጭብጥ እየተካሄደ ባለው የ2025 ፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ የአየር ንብረት ጥበቃን ለማራመድ አስፈላጊ የሆኑ ሶስት ቁልፍ የተግባር ነጥቦችን አፅንዖት ሰጥቼ አንስቻለሁ ብለዋል።
አንደኛ የአየር ንብረት ጥበቃ የገንዘብ አቅርቦትን የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት በቂ፣ ተገማች እና ዘላቂ በሆኑ ምንጮች ማረጋገጥ ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።
ሁለተኛ ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ እና የአኅጉሩን ወሳኝ ሥነምኅዳር ጥበቃ ለማድረግ በዓለም የኃይል ምንጭ ኢንቬስትመንት ሽፋን ውስጥ የአፍሪካን ድርሻ በአሁኑ ወቅት ካለበት ሁለት ከመቶ በ2030 ወደ ሃያ ከመቶ ማሳደግ ይገባናል በማለት ተናግረዋል።
እንዲሁም በሶስተኛ ነጥባቸው የብዝኀ ሕይወት ጥፋትን እና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ አፋጣኝ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ሲሉ አስገንዝበው፤ ይህም እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ሕዝባዊ ሥራዎችን በገንዘብ መደገፍን በዚህም ለየአካባቢው ኅብረተሰብ ከአድልዎ የፀዳና ፍትኀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን ያካትታል ብለዋል።