ከተረጂነት የተላቀቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም በሃላፊነት መንፈስ ሊሰራ ይገባል- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተረጂነት የተላቀቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና ጊዜው የሚጠይቀውን የለውጥ ርምጃ ዕውን ለማድረግ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አስገነዘቡ፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት አፈጻጸም ዙሪያ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዲሁም የሚኒስቴሩ አመራሮች እና ሠራተኞች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ÷በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያና ለኢትዮጵያ ያለው እንደምታ፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚና ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ፣ በመንግስት አገልግሎትና የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻይ ሥራዎች ላይ የታዩ ለውጦች፣ ዘላቂ ልማት፣ ማህበራዊ አካታችነትና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሯ የሀገርን ህልውና ለማስከበር የምንከፍለውን መስዋዕትነት ያህል ሀገርን ለማጽናትና ከተረጂነት ለመላቀቅ እንዲሁም ጊዜው የሚጠይቀውን የለውጥ ርምጃ ዕውን ለማድረግ ሁሉም በሃላፊነት መንፈስ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በልማቱ መስክ ሀገርን ማጽናት አሁን ያለው ትውልድ ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ በደም ያስከበርናትን ሀገር በላባችን ማጽናት ይጠበቅብናል ሲሉ ማሳሰባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡