ለሀገራዊ ዕድገቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጸጥታና ደኅንነት ሥራን በማስፈን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ በማድረግ ሂደት የፌደራል ፖሊስ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተመላከተ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በተገኙበት የበጀት ዓመቱ የተቋሙ የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡
በዚሁ ወቅትም ፖሊስ በፀጥታ እና ደኅንነት ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽዖ ለተገኘው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና መጫዎቱን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ተናግረዋል፡
ፖሊስ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር ተቀናጅቶ ባከናወነው ሥራ ከ15 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን አውስተዋል፡፡
በዚህም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ ጉዳት ማዳን ተችሏል ማለታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
የፖሊስ የማድረግ ዐቅም እያደገ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በሽብር፣ በተደራጁ ልዩ ልዩ ወንጀሎች፣ በታክስና በጉምሩክ፣ በፋይናንስና ንግድ ነክ ወንጀሎች ከ54 ቢሊየን 232 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ምርመራ መደረጉ በግምገማው ተነስቷል፡፡