ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በትብብር በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በትብብር በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር መግባባት ላይ ደረሱ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ጎብኝተዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላም ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው ጋር በትብብር በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ አቶ አድማሱ አስረድተዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት ዓላማ ላይ የጋራ መግባባት መኖሩን ጠቅሰው፤ የጋራ ዕቅዶችን በማቀድ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት የሚቻልበት ዐቅም መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚፈልግ ጠቅሰው፤ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ አመላክተዋል፡፡
ለዚህም የተጀመሩ የአከባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትብብር ለመሥራት ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን መምረጣችን ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ኮርፖሬሽኑ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ሕብረተሰቡ ሐሳብ እንዲሰጥ የውይይት መድረክ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡
የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት ውይይት በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ