Fana: At a Speed of Life!

ወደ ግብር ከፋይ ሰንሰለት ያልገቡ አካላትን ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወደ ግብር ከፋይ ሰንሰለት ያልገቡ አካላትን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮችና ሠራተኞች ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገራዊ እና በገቢ ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በዚህ ወቅት÷የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ በስኬት እንዲጠናቀቅ በእቅዱ ዙሪያ ከባለድርሻ አካለት ጋር ምክክር መደረጉ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል፡፡

ገቢ የመሰብሰብ ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ÷ ለነገ የገቢ ስኬት ምንም ትንፋሽ ሳንወስድ የትሪሊየን እቅዳችን ለማሳካት በትጋት መስራት አለብን ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው÷በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስኬት ካስመዘገቡ ተቋማት መካከል የገቢዎች ሚኒስቴር አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በቂ ገቢ መሰብሰብ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ይህንን ዕውን ለማድረግም የዘርፉ ስኬታማነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ወደ ግብር ከፋይ ሰንሰለት ያልገቡ አካላትን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት መሰጠቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.