ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ446 አቅመ ደካሞችና የልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤቶችን አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ446 አቅመ ደካሞችና የልማት ተነሺዎች የመኖሪያ ቤቶችን አስተላልፈዋል።
ከንቲባ አዳነች በቦሌ ክ/ከተማ 22 አካባቢ የተገነባ ባለ 4 ወለል ህንፃ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞችና የልማት ተነሺዎች በዛሬው እለት ቁልፍ አስረክበዋል፡፡
ከንቲባዋ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ በሁለንተናዊ መስኩ ነዋሪዎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ለዚህም ሰው ተኮር ተግባራትን በሁሉም ዘርፎች በማከናወን በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
ቤቶቹ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽንና፣ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እና የተለያዩ ባለሃብቶችን በማስተባበር 446 የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለአቅመ ደካሞችና የልማት ተነሺዎች ማስረከብ ተችሏል ብለዋል።
ከንቲባዋ በቤቶቹ ግንባታ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማትንም አመስግነዋል።
የመዲናዋን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
ለነዋሪዎች የተላለፉት መኖሪያ ቤቶች የቤት ቁሳቁስ የተሟሉላቸው እንደሆኑ ተጠቅሷል።