ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አዲስ ከተሾሙት የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር መንዳይ ሰማያ ኩምባ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አምባሳደር መንዳይ የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በቀጣይ በሀገራቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
አምባሳደር መንዳይ በበኩላቸው÷በሀገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
መሰል ጉብኝቶችም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው÷ለዚህም በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡