ስቅለት ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና ትሕትና በተግባር የተገለጠበት ዕለት ነው – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት አስተምህሮ ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና ትሕትናን በተግባር የተገለጠበት ዕለት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ገለፁ።
የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በእምነት ተከታዮች ዘንድ ታስቦ ውሏል።
በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መምህር ዳንኤል ይርጋ ቤተክርስቲያኗ ዕለቱን በስግደት፣ በጾምና ፀሎት ሥነ-ስርዓት የምታስበው ክርስቶስ ለሰው ልጆች ነፃ መውጣት የከፈለውን ዋጋ በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።
የክርስቶስ መስቀል ፍቅር፣ አንድነትና ይቅር ባይነት የተገለጠበት መሆኑን በማንሳት÷ ከክርስቶስ ፍቅርን እና ፍጹም ይቅር ባይነትን የምንማርበት የድህነት ቀን እንደሆነ ተናግረዋል።
የመፋቀር፣ መተሳሰብ እና የአብሮነትን ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሥነ መለኮት ትምህርት ተማሪ መላከ ሰማያት ገትዬ ቃኘው በበኩላቸው÷ የክርስቶስ ስቅለት እኛ የሰው ልጆች እርስ በርስ እንድንዋደድ የተከፈለ ዋጋ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ይህን በመገንዘብ እርስ በርሳችን በመዋደድ ትዕዛዙን መፈፀም አለብን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ስቅለት ተበድሎ ይቅር መባባል እንዳለ ከክርስቶስ የተማርንበት ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ መጋቢ ምስጢር ሰሀሉ አድማሱ ናቸው።