በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት ሊሆን ይገባል – ጉባኤው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት እና በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስገነዘበ።
ጉባኤው የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላልፏል።
በመልዕክቱም፥ በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና በመጠየቅ ማክበር እንደሚገባ ገልጿል።
በተጨማሪም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም በመጸለይ፤ ከትላንቱ ይልቅ ዛሬ የሰላም ሰው ለመሆን በመወስን እና ሰላምን ለማስፈን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
ጉባኤው በዓሉን አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና! (ማቴ 28፡6)
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ለመላው የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለ2017 ዓ/ም የጌታችን የመደኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ክብረ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን በአክብሮት ያስተላልፋል፡፡
ትንሳኤ በሃዘንና በጭንቀት እንዲሁም በክህደት ጸጸት እና ተስፋ በመቁረጥ ስብራት ቅስማቸው ለተሰበረባቸው የጌታችን የኢየሱስ ከርስቶስ ደቀመዛሙርት ብቻ ሳይሆን ለእኛም ለክርስቲያኖች ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ታላቅ ብርሃን የተሸጋገርንበት፤ የደም ዋጋ የተከፈለበት፤ ድንቅ የድል ክብረ በዓል ነው፡፡
የጌታችን እና የመደኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች፣ ወዳጆች እና ቤተሰቦች፣ የጭንቁን እና የሕማማቱን ወቅት በጥልቅ መከራ፣ በስጋት፣ ተስፋ በማጣት፣ በሃዘን እና በጭንቀት፣ አንዳዶችም ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀል ሞቱ በፊት ሲያስተምራቸው የነበሩበትን አንዳንድ ትምህርቶች እያሳቡ በሃዘን የተቆራመቱበት እጅግ ጥልቅ ጭንቀት እና ሲቃ ሕይወታቸውን ሰንጎ የያዘበት ሁኔታ ውስጥ ያለፉበት ወቅት ነበር፡፡
የእግዚአብሄር ዘላለማዊ ፈቃድ መፈጸሙ ግድ ነበርና አዳኛችን ብለው ኑሮአቸውን ትተው የተከተሉት፣ ሁሉ ነገራቸው የሆነው ጌታ አይናቸው እያየ በፊት ለፊታቸው ተገረፈ፣ ተናቀ፣ ተንገላታ፣ ተተፋበት በመጨረሻም የሰውን ልጅ የበደል እና የኃጢያት እዳ ለመክፈል በመስቀል ላይ በግፈኞች እጅ ተሰቀለ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ ስቃይ፣ ጣር እና ደም ካለፈ በኋላ በመስቀለ ሞት፣ በስቅላቱ የመጨረሻው ደቂቃ አብሮት በመስቀል ላይ ለተገኘው ፍርደኛ የዘላለም ሕይወት ተስፋን በመስጠት፤ ኤሎሄ ኤሎሄ እያለ በመጮህ፣ ላንገላቱት፣ ለወጉት እና ለሰቀሉት እጅግ በደለኛ ሰዎች ፍርድን ሳይሆን ምህረትን የለመነ፣ በኃጢያት ምክንያት ተራርቀው የነበሩትን እግዚአብሄር እና ሰውን ያቀራረበ፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ እግዚአብሄር እና ሰው የታረቁበት በዓለማችን ከተከሰቱት ታላላቅ ክስተቶች ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ እና ደማቅ ክስተት የተፈጸመበት ድንቅ ክብረ በዓል ነው፡፡
ቃሉን የማይረሳ እና የማያጥፍ፤ የተናገረውን ሁሉ ማድረግ የሚችል፤ እውነተኛው ታላቁ ጌታችን በሶስተኛው ቀን ከሙታን በመነሳት በጥልቅ ሀዘን፣ በተስፋ መቁረጥ እና ግራ በመጋበት ውስጥ ለነበሩት ታላቁን የብርሃነ ትሳኤውን ክብር እንዲያዩ አደረጋቸው፡፡
ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመቃብር ቦታ ሽቶ ለመቀባት በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ ሄደው ለነበሩት ሀዘንተኞች መልአክቶች ተገልጠው “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እርሱ ተነሥቶአል እዚህ የለም” (ሉቃ 24፡5—6) የሚል ደማቅ የትንሳኤ ብስራት በሃዘን ለተሰበሩት ተከታዬች ያበሰሩበት ክስተት ነው፡፡
ታላቅ የትንሳኤ ብስራት፣ ታላቅ ዜና፣ በከተማዋ ተሰማ፤ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋቸውን የሚያለመልም፣ በጥልቅ የሃዘን እና የፍርሃት ጨለማ ውስጥ ላሉት እውነተኛ ልባዊ ደስታ የሚሰጥ፣ የሕይወት አቅጣጫን የሚቀይር አስገራሚ የትንሳኤ ብስራት ተሰማ፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ እዳችንን ከፍሎ ከሞት ተነስቷል፡፡
በሌላ በኩል ይህ ታላቅ ክስተት ለጥቂት ጊዜ አሸናፊ በመሰለው በዲያብሎስ እና በተከታዮቹ መንደር ታላቅ መደናገጥ፣ ሽንፈት፣ ውርደት እና ማቅ የወደቀበት ጊዜ ነበር፡፡
ውድ ክርስቲያኖች የብርሃነ ትንሳኤ በዓል ለእኛ ለምናምን ታላቅ ትምህርት ያለው ድንቅ ክብረ በዓል ነው፡፡ ዛሬም ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች በሕይዎታችን፣ በአካባቢያችን እና በአገልግሎታችን ቢገጥመንም፤ ያጋጠሙን ፈተናዎች ክብደታቸው እንደ ሞት ጣር ቢሆንም እንኳን፤ በጽናት ከተጓዝን፤ ማለፋችን አይቀርም፤ እኛ የምንመካው እና የምንደገፈው በታላቁ ጌታ ይሁን እንጂ የትንሳኤ ሕይወት ዕለት ዕለት በግል እና በጋራ ኑሮአችን እየተመለከትን በለመለመ ሕይወት መጓዛችን የማይቀር ሀቅ ነው፤ ምክንያቱም የምናከብረው የትንሳኤ ክብረ በዓል ከሞት የመነሳት ሕያው ምስክር ነውና፡፡
ስለዚህ በፈተና ጽኑ፣ በትዕግሥት እና በጥበብ ተጓዙ፣ በፍቅር አገልግሉ፣ በይቅርታ ተመላለሱ እስከ ሞት ታገሱ ምክንያቱም የእኛ የክርስቲያኖች መሪና ምሳሌ የሆነው ታላቁ መድኃኒታችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሳኤው፣ እንዲሁም በምድር በነበረበት ጊዜ ሁሉ በማይለውጥ ቃሉና ተግባሩ ያስተማረን ግልፅ ትምህርት ይሄው በመሆኑ ነው፡፡
እርስ በእርሳችን እንዋደድ፣ የተቸገሩትን እንርዳ፣ የታመሙትን እንጠይቅ፣ የተጣሉትን እናስታርቅ ምክንያቱም የትንሳኤ ሕይወት መገለጫው በጎነት ነውና፡፡ የክርስትና መለያው ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይደለም፤ ታማኝነት እንጂ ክህደት አይደለም፤ ልግስና እንጂ ንፉግነት አይደለም፤ የምናምን እኛ ክርስቲያኖች ቃላችንን እና ተግባራችንን በማስታረቅ፤ እምነታችንን በተግባር በመተርጎም፣ የተከፈለልንን የሕይወት ዋጋ የሚመጥን ኑሮ በእግዚአብሄር ፀጋ ለእግዚአብሄር ክብር እና ለወገኖች ጥቅም የመኖር ኃላፊነት አለብን፡፡
በመላው ዓለም ለምትኖሩ ውድ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሙሉ በድጋሜ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን እያልን በዓሉን ስናከብር ሁል ጊዜ እንደምናደርገው የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት እና በመጠየቅ እንዲሆን፣ በተለይም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም በመጸለይ፤ ከትላንቱ ይልቅ ዛሬ የሰላም ሰው ለመሆን በመወስን እና ሰላምን ለማስፈን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ! በረከት ለመላው ሕዝባችን ይሁን! እግዚአብሄር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ