በዓሉን ስናከብርን በአቅማችን በመረዳዳት ይሁን- ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ ለመላው የክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም፤ በየዓመቱ የምናከብረው የትንሳኤ በዓል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ደኅንነት እስከ መስቀል ሞት ታዞ፣ ሞትን አሸንፎ፣ የሰው ልጆችን ወደ ብርሃን ያሻገረበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡
ይህን በዓል ስናከብርም የተከፈለልንን የፍቅር ዋጋ በማሰብ ድጋፍ ለሚሹ የማሕበረሰብ ክፍሎች በመድረስ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ሕጻናትን፣ አረጋውያንን እና ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ፤ በአቅማችን ልክ በመረዳዳት እና በመተሳሰብ በዓሉን እናክብር ብለዋል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡